Google

Thursday, June 08, 2006

Ethiopians have taken the past year's misery and oppression not only with resistance but sometimes humour and grace. The following is a collection of street jokes taken from different sources .
የዚያን መንደር ወጣቶች በድንጋይ ከፖሊስ ጋር ሲፋለሙ ለሁለት ሰዓት ያክል ቆዩ፡፡ ከዚያ የከተማ አውቶብስ ስለሚያቃጥሉ የሌላ ሰፈር ጎረምሶች ገድል በቴሌቪዥን ከታዬ በኋላ እነሱም አውቶብስ ለማቃጠል ፌርማታ ላይ ቆመው መጠበቅ ጀመሩ፡፡ ሲጠብቁ አውቶብስ አይመጣም፤ ሲጠብቁ አይመጣም፡፡ በመጨረሻ ፌርማታውን አቃጥለውት ሄዱ፡፡
............

የውስጥ ለውስጥ ፍተሻ በሚደረግበት ሰሞን ወታደሮች ወደ አንድ ደራሲ ወዳጃችን ቤት ገቡ፡፡ ቢፈትሹ፣ ቢፈትሹ ከመፃሕፍት በቀር ምንም አላገኙም፡፡
‹የጦር መሳሪያ የለህም?› አሉት
‹የለኝም›
‹ሌባ ቢመጣብህ በምንድነው የምትከላከለው?›
‹በካርል ማርክስ መጽሐፍ እፈነክተዋለሁ›
በመጨረሻ መታወቂያውን አይተው ትተውት ሲሄዱ ተከተላቸው፡፡
‹ለምንድነው የምትከተለን?›
‹አናቴ ላይ ትንሽ በሰደፍ እንድትወቅሩኝ ብዬ ነው›
‹ለምን?›
‹ሌሎች ከእናንተ የባሱ ሲመጡ የድርሻዬን ተደብድቤያለሁ ብዬ ምልክቱን አሳያቸዋለሁ›
.......

የዚያኛው መንደር ልጆች የዶዘር ጉማ አስፋልቱ ላይ ለማቃጠል ለሰባት እያሽከረከሩ ሲሄዱ ፌዴራል ፖሊስ ደረሰባቸው፡፡
‹ምን እያደረጋችሁ ነው?›
‹ልናስነፋው ወደ ጎሚስታ እየሄድን ነው›
‹ ባለፈው ጎሚስታ የገባ እስከአሁን አልተነፋም!›
...................
በአንድ ጋዜጣ ላይ የቅንጅት ተጠርጣሪ አይቶ የያዘ አስር ሺህ ብር እሰጣለሁ አለ የሚል ዜና መውጣቱ ይታወሳል፡፡ በኢንተርኔት ደግሞ እንዲህ የሚል ምላሽ ወጥቷል፡፡ የቅንጅቱን ተጠርጣሪ አይቶ እንዳላየ ላለፈ አንድ የቅንጅት ደጋፊ ባለሃብት ሃያ ሺህ ብር እንደሚሰጡ ይፋ አደረጉ፡፡
...........................

የግል ሬዲዮ ጣቢያ ለመክፈት የፈለገ ሰው ወደ ብሮድካስት ኤጄንሲ ይሄድና ሥራ አስኪያጁን ያገኛል፡፡ ሥራ አስኪያጁም ፈቃድ ለማግኘት መሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎች የሚያብራራ ዝርዝር ሕግ ይሰጡታል፡፡
በዝርዝር ሕጉ ፈቃድ ለማግኘት የሚከተሉት መስፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡
- ወንድ መሳይ ሴት
- ጥርሰ ፍንጭት
- ከዚህ ቀድሞ ቪ ኦ ኤ ውስጥ የሠራና በአጨቃጫቂ ሁኔታ የለቀቀ
.......................


ጥቂት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮች ቴዲ አፍሮን ይከሱታል፡፡ የክሳቸው መነሻ ‹ሼህ መንደፈር› የተሰኘው ዘፈን ነበር፡፡ ተከታዮቹ ቴዲ ሃይማኖታችን አራክሷል የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ ክሱ ለአቡነ ጳውሎስ ቀረበና ዘፈኑን አስመጡልኝ ብለው አደመጡት የሚከተለውን ውሳኔም ሰጡ፡፡
‹የቴዲ አፍሮ ዘፈን ሃይማኖታችንን አይፃረርም፡፡ ይልቁንስ ክርስቲያኑና እስላሙ በሀገሩ ተዋዶና ተከባበሮ እንዲኖር የሚገልጽ የሰላምና የፍቅር ዘፈን ነው፡፡ ባይሆን የሙዚቃውን ቢት አልወደድኩትም፡፡ ወይ አላስጨፈረ ወይ አላስቆዘመ›

Monday, May 29, 2006

Be'ewketu Seyoum is one of the most talented writers of his generation. At 25 he has already published two major works and written several short stories and essays on different newspapers and magazines. Ye'aba Bayifers Kushetoch(Ye'gan sir mastawoshawoch) is humour, fantasy and magic realism put in one. Here is the first two parts of the story. Laugh your hearts out. ጦሽ ብላችሁ ሳቁ
የጋን ስር ማስታወሻዎች
በበዕውቀቱ ሥዩም
አባ ባይፈርስ የእማ ሸንበቆ ደንበኛ ነበሩ፡፡ ጎረምሳ ሳለሁ ልጠጣ ስገባ ከሳቸው አጠገብ እቀመጣለሁ፡፡ አባ ባይፈርስ ከብርጭቆ ጋር እንጂ ከሰው ጋር ብዙም አይነጋገሩም፡፡ ሲያወጉ ግን ወጋቸው ይጥመኛል፡፡ እውነትና ገሃድ በሰለቸኝ ቁጥር በእማ ሸንበቆ ጋን እና በአባ ባይፈርስ አንደበት ሥር እሸሸጋለሁ፡፡
የዚያን ቀንም ሆን ብዬ ቆሰቆስኳቸው፡፡
‹አባ ባይፈርስ›
‹ወይ›
‹ከስድሳ አምስት በፊት ግሪክ ይኖሩ ነበረ የሚባለው እውነት ነው እንዴ;›
(እንዲህ ተብሎ እንደማያውቅ አውቃለሁ)
‹የለም ግሪክ አልሄድኩም›
‹እንግሊዝ ነበርሁ› አሉኝ ብርጭቆውን ካፋቸው ወደ ጤረጴዛው እየመሰሉ፤ ከዚህ በኋላ ዝም አልኳቸው፡፡ አፋቸውን ባይበሉባቸው ጠርገው ቀጠሉ፡፡
‹ከስድሳ አራት ዓመት በፊት እንግሊዝ ነበርሁ፡፡ መንግሥት ልኮኝ . . . ውሎዬ ተውንስተን ቸርችል ዘንድ ነው፡፡ እሳቸው መቼም ወጌ ጨዋታዬ ጥርሳቸውን ስለማያስከድናቸው ተጉያዬ አይጠፉም፡፡
ፓርላማው ሲሰለቻቸው ረግጠውት ወደእኔ ይመጣሉ፡፡ እኔ ጠጄን፣ እሳቸው ሻምባኛቸውን እየከለበስን እናወጋለን፡፡ አንድ ቀን ‹የቴዎድሮስ ሽጉጥ ግን እናንተ ዘንድ ነው;› ብዬ ጠየቅኋቸው ቸርችልን፡፡ ‹አዎ ታጥቄው ምዞረው እሱን ነው› አሉኝ፡፡ ተቀብዬ አየሁት፡፡ ግን ማዬት አይበቃም ሁለት ጥይት አጎረስኩና ጆሮዬ ላይ አነጣጥሬ ‹ብው› አረግሁት፡፡ ጥይቱ በግራ ጆሮዬ መሐል ለመሐል ሄዶ በቀኝ በኩል ወጣና የቸርችልን ጠባቂ ገንድሶ ጣለው፡፡ ‹ተረፍክ?› አሉኝ ቸርችል፡፡
‹ምን እሆናለሁ? ይልቅ ጆሮዬ ሥር ተጋግሮ የከረመውን እፍኝ ሙሉ ኩክ ወከወከልኝ . . .› አልኳቸው፡፡ የገረመኝ ቴዎድሮስ በዚህ ሽጉጥ ራሱን ገደለ መባሉ ነው፡፡ በኋላ ሳጣራ ቴዎድሮስ የሞተው ሴባስቶፖል የተባለውን መድፍ ጠጥቶ መሆኑን ደረስኩበት፡፡
ቸርችል በጭውውታቸው ወቅት በደንገጡሮቻቸው ተከብበው ትምባሆ እያጨሱ ነው፡፡ ትምባሆ ሲያጩ በጭሱ ክብ መሥራት ያዘወትራሉ፡፡ የሚገርመው የደንገጡሮቻቸው አምባር በሙሉ በትምባሆው ጭስ መሠራቱ ነው፡፡
ቸርችል መቼም የሂትለር ጠበኛ ናቸው፡፡ አቤት ስለ ሂትለር ሲነሳ የሚሆኑት አኳኋን! ፊታቸው እንደ ወፍ ጥርስ ይነጣል፡፡
ሂትለር አይሁዶችን ገድሎ ፀጉራቸውን የፍራሽ መሥሪያ እንዳደረገው ሲነግሩኝማ ፊታቸው እንደዝሆን ክንፍ ይቀላል፡፡
ታዲያ ጊዜ መቼም ደግ ነው ሂትለር ተገደለ፡፡ ቸርችልም ሊበቀሉት ሲፈልጉ ተከንፈሩ በላይ ተአፍንጫው በታች ያለችቱን ጠጉር ነጭታችሁ አምጡልኝ ብለው ባገሪቱ የታወቁትን ባርባሪዎችን አዘዙ፡፡ አመጡላቸው፡፡ ከዚያ አጫጭር ፀጉር ያላቸው የእንግሊዝ ቆነጃጅት በሂትለር ሪዝ ጠጉራቸውን እያስረዘሙ እንዲዋቡ ፈቀዱላቸው፡፡ ከዊግ የተረፈው የሂትለር ሪዝ የእንግሊዝ አዝማሪዎች መሰንቆ መሥሪያ ሆነ፡፡
ቸርችል መቼም የሚገርሙ ሹማምንትም ነበሯቸው፡፡ አንድ ሹማቸው የባርላማ አባል ሲሆን ሰላሳ እጅ አለው፡፡ ከፊት አሥራ አምስት ከኋላ አሥራ አምስት . . .
መጀመሪያ ይሄን ሰውዬ እንዲህ የቀረቡት ለምንድነው; ብዬ አስብ ነበር፡፡ በኋላ ግን ነገሩ ተገለፀልኝ፡፡ ባርላማ እሱን ይዘውት ከገቡ በድምጽ ብልጫ ፓርቲቸው ያሸንፋል፡፡
መቼም በባርላማ ህግ ማሸነፍ ማለት በእጅ ቁጥር መብለጥ መሆኑን ታውቃለህ፡፡ ያኔም እንደዛሬው እጆች እንጂ ሰዎች ከቁጥር አይገቡም ነበር፡፡
የእንግሊዝ ገድሌ ተብሎ ተብሎ ሚያልቅ አይደለም ልዤ . . . ተቸርችል ያሳለፍኩት ጽፈውት ስንክሳርን የሚካክል አርባ ጥራዝ ወጣው፡፡ ኋላ መላው እንግሊዝኛ እንዳያልቅ ሰግተው የፈረንሳይን ሊቃውንት ትብብር ጠየቁ፡፡ ፈረንሳዮችም ፈረንሳዮች ናቸው፡፡ ብዛቱን ገምተው ይሄን እንኳ በስዕል እንጅ በጽሁፍ አንሞክረውም ብለው አፈገፈጉ፡፡
በስልሳ አምስት ነው እንግሊዝን ለቅቄ ወደ አገሬ የመጣሁት፡፡ ቸርችል አየር ማረፊያ እየሸኙኝ ስንላቀስ አራት ሰዓት ፈጀብን፡፡ አውሮፕላኑ ብድግ አለ፡፡ ቸርችል ብስጭትጭት ብለው በከዘራቸው ክንፉን ስበው ወደ ምድር ባይመልሱት ኖሮ ትቶኝ መሄዱ ነበር፡፡
‹. . . በል ልጄ ጋቢና ግባና ተቀመጥ› አሉኝ ደጉ ቸርችል፡፡ ትቻቸው ወደ ላይ ወጣሁ፡፡ ከላይ ሆኜ እንግሊዝን ሳያት ደቅቃለች፡፡ የቸርችል ባርኔጣ የቤተክሲን ጣሪያ መስሎ ሲታየኝ ሆዴ ቦጭ ቦጭ አለብኝ፡፡ የሆድ ቦጭቦጭታ አደጋ ጠቋሚ ኑሯል፡፡ መንገድ ላይ አውሮፕላኑ እንደ ፊኛ ይነፋ ጀመር፡፡ ፓይለቱ ‹ጎበዝ በያዛችሁት የምሳ እቃ የተቻላችሁን ንፋስ እየዘገናችሁ ቁልቁል እንድትደፉ በማክበር አሳስባለሁ› አለ፡፡ ያለውን አደረግን፡፡ ጎጃም ስንደርስ ሌላ አደጋ ገጠመን፡፡ አይሮፕላኑ ከወፍራም ተርብ ጋር ሄዶ ቢላተም ግማሽ አካሉ ቦነነ፡፡
‹ፓራሹት ይዛችሁ ውረዱ› ብሎ ፓይለቱ ጮኸ፡፡ ከኋላ ወንበር የተቀመጡት ፓራሹት ለብሰው ቁልቁል ዥው እያሉ ወርደው ከታች ካለ የደመና ጉማጅ ላይ ተከሰከሱ፡፡ ይገርምሃል አጥንታቸው እስከ ዛሬ ድረስ በመብረቅ መልክ ይወርዳል፡፡
ይሄን ሳይ መላ መታሁ፡፡ ፓራሹቱን ትቼ መውደቂያዬን እፈልግ ዠመር፡፡ ዝቅ ብዬ ሳይ ያባቶቼ አገር እነማይ ደርሻለሁ፡፡ ደግሜ ዝቅ ስል እብድ የሚያህል የጤፍ ክምር አየሁ፡፡ አነጣጥሬ ወደቅሁበት፡፡ ቡን አለ፡፡ ኋላ ቢታይ ፍሬ ወዲህ ገላባ ወዲያ፣ በመሀል እኔ ተገኜሁ፡፡ አባቴ ገርሞት ‹በሰውና በከብት አንድ ሳምንት የሚፈጅብኝን ባንድ ልጄ ገላ ወቃሁት› ብሎ ፈነጠዘ፡፡
ተዚያ ከእነማይ አብማ ገብቼ ጠላዬን እየጠጣሁ ስኖር ድርቅ ገባ፡፡ ስድሳ አምስት ግድም መሰለኝ ዘመኑ፡፡ ሳይ ህጣናቱ ያልቃል . . . ሳይ ህዝቡ ያልቃል . . . ሆድ ብሶኝ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ እንባዬ እየገነፈለ ሲወርድ በመዳፌ ተቀበልሁትና ሽቅብ አጎንሁት፡፡ ሰማዩ ላይ ሄዶ ተለጠፈ፡፡
ይገርማል የግራ ዓይኔ እንባ ጭጋግ የቀኙ ደመና ሆነ፡፡ አመሻሽ ላይ ይዘንብ ዠመረ፡፡ ሕዝቡ ‹እልል የልቦናችንን አይቶ ዝናብ ላከልን› ብሎ አመሰገነ፡፡ ውለታዬን ቢዘነጉ አዘንኩባቸው፡፡ አዘኔ የፃድቅ ሆኖ ፈጣሪ ሰማኝ፡፡ ጤፍ የዘሩበት መሬት ቀይ ሽንኩርት አበቀለ፡፡
እንግዲህ ወገኖችህ ሽንኩርት በመተሩ ቁጥር የሚያለቅስቱ በዚህ ምህኛት ነው፡፡
በዓመቱ የጎጃም ድርቅ ቀነሰ፡፡ የወሎ ድርቅ ባሰበት፡፡ የነዜ ቴሌብዝዮን ነበረኝ፡፡ ረሃብተኛው ግልብጥ ብሎ ሲሰደድ በቴሌቪዚዮን አየዋለሁ፡፡ እዬዬ ብዬ አዝኜ በዜግነቴ አንድ ነገር ለማድረግ ቆረጥሁ፡፡ ሁልዜ ማታ ማታ የዜና ሰዓት ሲደርስ ገብስ ቆሎ በቁና፣ ጠላ በቅምጫና ቴሌቪዚዮኑ አጠገብ አስቀምጣለሁ፡፡ በቴሌቪዚዮኑ ውስጥ ያሉት ረሃብተኞች ያንን ሲያዩ እጃቸውን ሰደው ተገብስ ቆሎው ትንሽ ዘግነው ከቅምጫናው ትንሽ ጠጥተው እጅ ነስተው ይሄዳሉ፡፡ መቼም ሁሉንም መቀለብ አይቻልም፡፡ እህል ውሃው ሲያልቅ ቴሌቪዚዮኔን አጠፋዋለሁ . . . አይ ጉድ . . . ያ ሁሉ እንደዋዛ ቀረ . . .› ብለው አባ ባይፈርስ ወደ ጠላው ተመለሱ፡፡
2 -
አባ ባይፈርስ እማ ሸንበቆ ቤት በረጅም ብርጭቆ መራራ ጠላ እየጠጡ ያወጉት ወግ ቀጣይ ክፍል የሚከተለው ነው፡፡
‹ወደ መጨረሻ ዘመናቸው ጃንሆይ ቁጡ ሆኑ፡፡ የሕዝቡንም አመጽ ባመጽ ልግታው ብለው ተነሱና ኃይል ሰደዱ፡፡ ጎጃምና ባሌ ቢያምጽ ባይሮብላን ቀጠቀጡት፡፡ እኔ እዚህ አብማ ተቀምጩ ጠላዬን እየከለበስኩ ሳይ የጠቅል አይሮብላኖች ጉንቻን ይቀጠቅጧታል፡፡ ጎንቻ የወደቀው ቦምብ ፍንጣሪው ሲከንፍ መጥቶ እምጠጣበት ዋንጫ ሥር ጥልቅ አለ፡፡ እስቲ እስቲ ብዬ ብቀምሰው የምኒልክ ጠጅ የምኒልክ ጠጅ ይላል፡፡ ተዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠላ ስጠጣ ትንሽ ባሩድ ታላረግሁበት አይጥመኝም፡፡ ወደ ጥንተ ነገሬ ልመለስና የጦር አይሮብላን አገሩን ሲያነደው ሳይ ሆድ ባሰኝ፡፡ ጥቃት መዘመዘኝ፡፡
እንዳይቀር ነዶ
እንዳይሄድ ወልዶ
እንዴት ያለ ዥግና ቀረ ተጨማዶ
ብዬ ፎከርኩና ወጣሁ፡፡ ሽቅብ ስመለከት አይሮብላን አብራሪው አይሮብላኑን ሾላ ዛፍ ላይ አሳርፎ እንቅልፉን ይለጥጣል፡፡ ቀስ ብዬ ወደ ዛፉ ወጣሁና ጅራቱ ላይ ሙዳ ሥጋ ቋጥሬበት ወረድኩ፡፡ ባይለቱ እንቅልፉን ጨርሶ አይሮብላኒቱን ከሾላው ዛፍ ላይ አስነስቶ ሲከንፍ ሥጋውን ያዩ ጥንባሳዎች ተጠራርተው መጥተው ከበቡት፡፡ ሰማዩ ሁላ አሞራ ሲሆንበት በምን ሰማይ ይንዳ; እዚያ ሆኖ ሲተናነቅ ሳየው መቼም ወገን ነውና አሳዘነኝ፡፡ ረዥም ሃረግ ወረወርኩለት፡፡ በዚያ ተንሸራቶ ወረደ፡፡
ይገርምሃል ዠግንነትና አመጽ በዘራችን ነው፡፡ አሁን የኔ ወንድም በሪሁን አለልህ . . . ዓይነ ሥውር ነው፡፡ ግን አነጣጥሮ ሲተኩስ የዝንብ ግንባር ይረቅሳል፡፡ ጣሊያኖችን መድረሻ አሳጣቸው፡፡ ማረኩትና ሞት ፈረዱበት፡፡
ኋላ ሕዝቡን በነቂስ ጠርተው ወንድሜን በየኔትሪክ ወንበር አስቀመጡት፡፡ አስቀምጠውት ሲያበቁ የኮነረንቲውን ሶኬት በሰርኑ ውስጥ ከተቱና Switch on የሚለውን ተጫኑት ምን የሆነ ይመስልሃል@ . . . ዓይኑ በራለት፡፡ ለካ መግደያ መስሏቸው ማብሪያውን ተጭነውት ኑሯል፡፡ አንድም ሳይቀር ፈጃቸው፡፡
በስድሳ ስድስት ተማሪው ጃንሆይ ይውረዱ ይውረዱ አለ፡፡ እሺ አሉና ተሥልጣን ወረዱለት፡፡ ቀጥሎም ይውረዱ ይውረዱ አለ፡፡ እሽ ብለው ወደ መቃብር ወረዱለት፡፡ ተማሪ መልአክ ቢሆን ኖሮ ወደ ሲኦል ይውረዱ ይል ነበር፡፡
ተማሪ ታመረረ፣ በግ ተበረረ አንድ ነው፡፡ ‹መሬት ላራሹ› እያለ ተመመ፡፡ ተዚያ በኋላ ‹መሬት› ሳይሆን ‹ምሬት› ላራሹ ተደነገገ፡፡ እሱን ልተወውና ስለኔ ገድል ልንገርህ፡፡ ጃንሆይ ሲወድቁ ኮሚኒስት ሆኜ ኢምፔርያሊዝምን አስበው ጀመር፡፡ መስከረም ሁለት ቀን ተራማጆችን እየመራሁ ሰልፍ አደርጋለሁ፡፡ ቀኑን ሙሉ ኢምፔርያሊዝም ይውደም› እያልሁ ክንዴን ስወረውር ዋልኩ፡፡ አመሻሽ ላይ ‹ኢምፔሪያሊዝም ይውደም› ብዬ ስፈክር እጄ ከትከሻዬ ተነቅሎ ሽቅብ ወጣ፡፡ ቀና ብዬ ባይ ባቅራቢያው ታለ ባሕር ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ሳይደግስ አይጣላም፣ አንድ ተራማጅ ጉሬዛ አንስቶ ቁልቁል ወረወረልኝ፡፡ ተቀብዬ ከትከሻዬ ጋር በመርፌ ቁልፍ አያያዝኩና ሰልፌን ቀጠልኩ፡፡›
አባ ባይፈርስ ከፖለቲካ ውጭ ያለውን ሕይወታቸውን ሲነግሩኝ ‹ከፖለቲካ ውጭ አደንና ውሃ ደስ ይለኛል፡፡ ከአደን ሁሉ ደስ የሚለኝ ቆቅ ማደን ነው፡፡ አንድ ቀን አንዲቱ ቆቅ ዓይኗን ጨፍና ስታሰላስል ከኋላዋ ዝግ ብዬ አፈፍ አርጌ ያዝኳት፡፡ ክው ብላ ደነገጠች፡፡ በድንጋጤ ሰባት እንቁላል ዘረገፈችልኝ፡፡ እንቁላሎቹን በካፖርት ኪሴ ከትቼ እሷን ለቀቅኳት፡፡ ኋላ በኪሴ ውስጥ እንዳለ ረስቼው ወር አልፎታል፡፡ አንድ ቀን ሳንቲም አወጣ ብዬ እጄን ኪሴ ብከት ሰባት የቆቅ ጫጩት ይዞ ተመለሰ፡፡ ይገርምሃል የጫጩቶቹ መልክ ደግሞ ቁጭ የካፖርቴን ቀለም ይመስላል፡፡
መቼም እንደ ዋና ደስ የሚለኝ ነገር የለም፡፡ ልጅ እያለሁ፣ ዋና እወዳለሁ፡፡ ግን ማን ያስተምረኝ; አባቴን ብለምነው ተው ይቅርብህ ሰምጠህ ትሞታለህ ብሎ አስቦካኝ፡፡
ኋላ መላ ፈለግሁ፡፡ መቼም አንጎሌ ጥይት ነው፡፡ መላ ከተፍ አለልኝ፡፡ እንዴት ነው; በለኝ፡፡ ትልቅ ባህር ውስጥ እገባና ብዙ ውሃ እጠጣለሁ፡፡ ሆዴ ሲሞላ ግዙፍ አሳ ከነነፍሱ እውጥበታለሁ፣ ይገርምሃል አሳው ሆዴ ውስጥ ሲዋኝ እኔንም ተሸክሞኝ ይሄዳል፡፡ የባህር ጉዞ ሁልጊዜ አይዋጣም፡፡ ብዙ አደጋ አለው፡፡ አንድ ቀን ባህሩን እንደሰንበሌጥ ስሰነጥቀው አገር የሚያህል አሳ ነባሪ አፉን ከፍቶ ተቀበለኝ፡፡ ሰተት ብዬ ገባሁ፡፡ መግባቴ በጀኝ፡፡ በሆዴ ውስጥ የነብዩ ዮናስን በርኖስ አገኘሁት፡፡ የነብዩ ዮናስ መሆኑን በምን አወቅህ; በለኝ፡፡ በርኖሱ ኮሌታ ላይ በነነዌ ጊዜ የተሠራ ሜድ ኢን ነነዌ የሚል ጽሁፍ አነበብኩ› አሉና ወደ ጠላው ተመለሱ፡፡